እኛ ሁላችን በክርስቶስ ደም ድነናል፡፡ በአንተ/በአንቺ?

በባህር ዳር ደሴ ካቶሊካዊ ሰበካ በኮሙኒኬሸን ቢሮና በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አስተባባርነት የምዕመናን፣ የሰራተኞችና የተማሪዎች “ደሜን የወገኔን ሕይወት ለማትረፍ” በሚል መሪ ቃል የደም ልገሳ ፕሮግራም ተካሄዷል፡፡

ግንቦት 20፡2009ዓ.ም በባህር ዳር ኪዳነ ምሕረት ካቶሊካ ካቴድራል ቅጥር ግቢ ዉስጥ በተደረገው የድም ልገሳ ፕሮግራም ላይ የሰበካው ጳጳስ ብፅዕ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ማቴዎስ ተሳትፈዋል፡፡ በሕይወት ዘመን ታላቅ ስጦታ በሆነው የደም መለገስ ተግባር ተሳትፈዉ የእናቶችንና የሕጻናትን ሞት ለመቀነስ እንዲሁም በደም እጦት ለአደጋ የሚጋለጡትን ወገኖቻችውን ለማዳን የሚደረገውን ርብርብ ማገዝ በመቻላቸዉ መደሰታቸዉን በባህር ዳር ደሴ ካቶሊካዊ ሰበካ ሐዋሪያዊ ስራ ማስተባበሪያ ቢሮና የሰበካው ጳጳስ ብፅዕ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ማቴዎስ ገለፁ፡፡

ብፅዕ አባታችን አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ማቴዎስ በደም ልገሳዉ ወቅት ለበጎ ዓላማዉ ተሳታፊ ለሆኑ ሰራተኞች፣ ምዕመናን፣ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደገለፁት በዚህ ታላቅ በጐ ሥነ ምግባር ላይ ወደ 50 የሚጠጉ ካቶሊካዊያን ደም በመለገሳቸው  ደስታና ኩራት ተሰምቶኛል ብለዋል፡፡ ደም መለገስ ታላቅ የሰብአዊ ተግባር  ስለሆነ ማንኛውም ሰው ዛሬ የገለሰው ደም መቼና የት ቦታ ለማን እንደሚያገለግል ስለማይታወቅ በደም እጦት ምክንያት የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ በቀጣይም መሳተፍ እንዳለባቸው ብፅዕነታቸው አሳስበዋል፡፡

የደም ልገሳ ሥነ ሥርዓቱ እንዲካሄድ ያስተባበሩት የሰበካው ኮሙኒኬሸን ቢሮ ሃላፍ ወጣት ፋሲካ ላቾሬና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አስተባባሪ ተማሪ ፅዮን ወልደ ትንሳኤ (እጩ ዶክቴር) በበኩላቸው ይህ በጐ ተግብር ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በባህር ዳርና በመላው ሰበካ በካቶሊካዊያን ዘንድ የበጐ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች ቁጥርን ለማበርከት የዛሬው ጅምር ቀጣይነት እንደሚኖረው ዕምነታቸዉን ገልፀዋል፡፡ አንዳንድ የዚህ በጐ ዓላማ ተሳታፊ የሆኑት ምዕመናንና ተማሪዎች በበኩላቸው ደም ከተሰጠ በኋላ ወዲያው የሚተካ ስለሆነ በተፈጥሮ የሚሰጠንን ፀጋ ለሌሎች ለተቸገሩ ወገኖቻችን እንዲድኑበት በመለገሳችን በጣም ደስተኞች ነን ካሉ በኋላ በየሶስት ወሩ የደም ልገሳ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

በመጨረሻም የካቶሊካ ቤተክርስትያን ለባህር ዳር ከተማና ለአካባቢ ነዋሪዎች ከምንም በላይ ለሰው ልጅ ክቡርነትና የሰውን ሕይወት ለማዳን የምታደርገው ስራ ከፍተኛ ስለሆነ ከዚህ ቀደም ካከናወነቻቸው ማኅበራዊ ኃላፊነቶች መካከል ጥራት ያለውን ትምህርትና ጤና ተቋማትና ለማህበረሰብ በማበርከት፣  ህፃናትን በማስተማርና መበለቶችን በመደገፍ ተግባር ስታከናውን የቆየች ሲሆን፤ ለወደፍትም  ይህ በጎ ተግባር በሁሉም ዘንድ እንዲያድግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ለጋሾች ገልፀዋል፡፡

    Translate »