የ2009 ኢየሱስ የትንሣኤ በዓልን መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

“ሕያው የሆነውን ኢየሱስን በሙታን መካከል ስልምን ትፈልጉታላችሁ እርሱስ እዚህ የለም ተነስቷል” /ሉቃስ 24፡5-6/
በክርስቶስ እጅግ የተወደዳችሁ በክልላችን የምትገኙ ምዕመናን፣ ካህናት፣ ወንዶችና ሴቶች ደናግላንና መነኮሳት እንዲሁም በጎ ፍቃድ ላላችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፡፡ ሁላችሁም እንኳን ለ2009ዓ.ም የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ በሰላም አደረሳችሁ እላለሁኝ፡፡ የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ ለሰው ልጅ በሙሉ የተስፋ ድል የሚያውጅልን ነው፡፡ ይኸውም የሰው ልጅ በኃጢያት ምክንያት ወደ ዓለም የገባው ሞት የመጨረሻ ፍርሃቱ ነው፡፡
ቃሉ፡ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወሰን እንዳለው ዛሬ ምንም እንኳን በምድር ላይ የሰው ልጅ መከራው የበዛ ቢሆንም እነሆ “ሞት ሆይ ድል መንሳትህ የት ነው፤ ሞት ሆይ ሰውን የምትጎዳበት ኃይል የት ነው?(1ቆሮ 15፡55)” በማለት ሐዋሪያው ጳውሎስ የጠየቀው ጥያቄ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤን በማየቱና መከራዎቻችን ሁሉ እኛን የመጉዳት አቅም የሌላቸውና ክርስቶስ ከእነዚህ ሁሉ ትንሳኤያችን መሆኑን በማየቱ ነው፡፡ በማለት በትንሳዔው ኃይል ድል በመንሳት ተስፋችን እንደለመለመ ይገልጻል፡፡ ለኛ ይህ የነፍሳችንን ስጋት ያጠፋል፡፡ ለስጋችንም ትልቅ የኃይል መታደስና መነቃቃት ይሆናል፡፡
እንግዲህ ነፍሳችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በከፈለው ዋጋ ምንም እንኳ ያረፈች ብትሆንም ስጋችን የማህበረሰባችን ጉስቁልናና ያልተስተካከለ የኑሮ ማጉረምረም የእኛን ስራ ይጠብቃል፡፡ የሰለሉ እጆቻችን በርትተውና ነቅተው ካልሰሩ ከድህነት ለመውጣት በግልም ሆነ በማህበረሰብ ደረጃ በእጃችን ካልሰራን፤ እርስ በርሳችን ካልተደጋገፍንና ካልተረዳዳን፤ ካልተስማማንና ካተመካከርን እንዲሁም ካልተቀባበልን ያለእኛ ፍቃድ የፈጠረን አምላክ ዛሬ ያለእኛ ፍቃድ ሊያድነን ስለማይችል እርስ በርሳችን እንጠፋፋለን፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም ኃጢያት ሳይኖርበት ከፍቅሩ የተነሳ የእኛን ድካም ለመሸከም ከወደደ እኛም ከእርሱ ተምረን ለበዓል ሰሞን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያት እርስ በእርሳችን በፍቅር ተያይተን ልንረዳዳ ይገባናል፡፡
ትንሳዔ የፍፁም ፍቅርና የፍፁም ልግስና ኃይል ውጤት ነው፡፡ ስለዚህም የዕብራዊ ጸሐፊ እንደጠቀሰው “በፍቅርና በመልካም ስራ ነቅተን እንድንኖር አንዱ ሌላውን ያሳስበው… ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ ይህንን ነገር ከፊት ይልቅ በይበልጥ አድርጉ፡፡ ዕብ 10፡ 24-25” እንደሌሎች የዓለማችን ክፍሎች የሀገራችንም ህዝብ ብዛት መጨመር የችግር ምክንያት መሆኑ ቀርቶ የእድገት ግብዐት ሊሆን ይገባዋል፡፡ እንደሀገር በጋራ እድገት የተወጠኑ እንቅቃሴዎች ላይ በሙሉ ኃይልና በሙሉ ልብ መተባበራችን የኑሮዎችንና በክፋት ላይ ለሚኖረን ድል ለፋሲካችን ዋስትናችን ነው፡፡
ከድህነት፣ ከበሽታ፣ ከረሃብና ከጦርነት ባልታናነሰ ሁኔታ ሕይወትን በከፍተኛ ቁጥር እየቀጠፈ ያለውን የመኪና አደጋ ትኩረት በመስጠት እግረኞችም ሆኑ አሽከርካርዎች ጥንቃቄ እንድናደርግ አባታዊ ምክሬን እለግሳለሁ፡፡ በቅርቡ በእዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪዎች ላይ በደረሰው አደጋ ቤተሰቦቻቸውንና ልጆቻቸውን ላጡ ወገኖቻችን የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እየገለፅኩ በሐዘናቸው ከጎናቸው ለነበሩት ሁሉ በባህር ዳር ደሴ ሰበካ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና በራሴ ስም ልባዊ ምስጋና እያቀረብኩ ለወደፊትም ሁላችንም ለተጎዱት ስዎች ከጎናቸው በመሆን እንድናግዛቸው ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ ለሞቱትም እግዚአብሔር መንግስቱን እንዲያወርሳቸው ቤተክርስቲያን ትጸልያለች፡፡
በመጨረሻም አልጋ ላይ ለሚገኙ ሕሙማንና ለህግ ታራሚ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በተላይም የክልላችን ሕዝቦች እንኳን ለ2009ዓ.ም ብርሃነ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁ እላለሁ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
    Translate »