የ2009ዓ.ም የገና በዓል መልዕክት

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
የተከበራችሁ የሀገረ-ስብከታችን ካህናት፣ደናግል፣የቤተክርስቲያኗ አገልጋዬች ምዕመናንና እንዲሁም በጐ ፈቃድ ያላችሁ ኢትዮጲያውያን በሙሉ ልዑል እግዚአብሔር እንኳን ለ2009 ዓ.ም የጌታችን የመድሐኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደቱ በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡ “ህፃን ተወልዶልናል፣ወንድ፣ልጅም ተሰጥቶልናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ፣መካር፣ኃይል አምላክ የዘላለም አባት፣ የሠላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፡፡(ኢሳ9፡6) ይህ ነቢዩ ኢሳያስ የሚናገርለት ሕፃን የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ የማርያም ልጅም ነው፤ ኃይሉም በኃብት ክምችት ላይ የተመሠረተ የዚህ ዓለም ኃይል አይደለም፡፡ “ኃይሉ የፍቅር ኃይል ነው፡፡ ይህ ኃይል ሰማይና ምድርን የፈጠረ ኃይል ነው፡፡ ለፍጥረት ሁሉ ሕይወትን የሰጠ ኃይል ነው፡፡ ይህ ኃይል ባልና ሚስት “እናትና አባታቸውን ይተዋሉ ሁለቱም አንድ ይሆናሉ” የተባለላቸውን ስራ የስራ ሁለቱን ተቃራኒ ፆታ ያጣመረ ኃይል ነው፡፡ ከሁለቱም አንድ ሕይወት እንዲወለድ ያደረገ፣በደልን ይቅር ያለ፣ከጠላት ጋር እርቅን ያበጀ ክፋትን ወደ በጐነት የለወጠ ኃይል ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ኃይል ነው፡፡ ይህ ፍቅር ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የራሱን ክብር ትቶ ሰው እንዲሆን በመስቀል ላይ ሕይወቱን እንዲሰጥ፣እና፣ከሞትም እንዲነሳ ያደረገው፡፡

ዛሬም ይህን የመሰለ ራስን የተወ የአገልግሎት መንፈስ ነው፤ለዓላማችን የእግዚአብሔር መንግስት፣የፍትህና የሰላም መንግስት ሊያውጅልን የሚችለው፡፡ ለዚህም ነው በሕፃኑ ኢየሱስ መወለድ ሰዓት የተሰማው የመላዕክት መዝሙር፡- በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሁሉ ሰላም ይሁን (ሉቃ 2፡14) እነሆ ዛሬ በጌታ ልደት በገና በዓል ይህ በሰማይ ካለው ከእግዚአብሔር ኃይል የሚመነጨው ሰላም እስከ ምድር ዳርቻ ተሰምቷል፡፡ በተለይም የጦርነት ቀጠና ከሆኑት የዓረብ ምድርና ሌሎች የአለማችን ክፍሎች በአስከፊ ግጭት ውስጥ ተዘፍቀው ላሉ ሰላምን እጅግ የሚናፍቁት ሁሉ ይህ የሰላም ንጉስ ባመጣው ዜና ይደሰታሉ፡፡ ሰላም በሶሪያ በጦርነትና በስደት ጭንቀት ላሉት ወንዶችና ሴቶች፤ሰላም በተወደደችው የእየሩሳሌም ምድር ለሚገኙ ወንዶችና ሴቶች፤ እግዚአብሔር  እነዚህ የእስራኤልና የፍልስጤም፣ሕዝብ አዲስ ምዕራፍ እንዲከፍት በማመን እንዲሁም ኢራቅ፣ሊባኖስና የመን ጦርነት ግፍ፣ አሸባሪነት ጠፍቶ እንደገና አንድነትንና ስምምነትን እንዲያገኙ በአፍሪካ በሩቅ ምስራቅና በሌሎችም የአለም ክፍሎች ለሚገኙ የሚያውጅ፣የሚጠራ፣የሚጋብዝና የሚያስችልም ቀን ነው፡፡

እነሆ እኛም በሃገራችን ሰላም ሲደፈርስ የሚያስከትለውን ውጤት ምን እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያቶች አይተናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው በሰማይ ያለው ሰላም እንዲሁ በምድርም ያገኛልና ሃገራችንም የሃይማኖት ሃገር ሕዝባችንም ያለ ልዩነት የሚያምን ሕዝብ ስለሆነ ሰላማችንን ለማረጋገጥ ሁላችንም የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ለበጐ ነገር እንሽቀዳደም፤ በቅንነትና በሃገር ዕድገት ሃሳቢነት እና ለእያንዳንዱ ዜጋ በጐነት ጥንቃቄ ላይ የተመሠረተ የፓለቲካ ተሳትፎ እንድናዳብር እነሆ ይህ የሰላም አምላክ በዚህ የገና በዓል ይጠራል ሰሚ ጀሮ ያለው ይስማ፡፡ በመጨረሻም በዓላችን እውነተኛና አምላክ የሚወደው እንዲሆን ድሆችን፣ሕሙማንን፣ የሕግ ታራሚዎችን፣የእኛን ድጋፍ እንደ አቅማችን የሚያስፈልጋቸውን የሚያስብ እና ብክነት የሚያስተናግዱ እንዳይሆን፤ እያሳሰብኩ የተባረከ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት
በዓል ያድርግልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጲያን ይባርክ

+አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ማቴዎስ
የባ/ዳር ደሴ ካቶሊካዊ ሰበካ ጳጳስ

Translate »