Message from H.E Bishop Lisanuchristos

+++++++++Bishop of Eparchy of BahirDar-Dessie+++++++++

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የባህር ዳር ደሴ ሀገረስብከት ጳጳስ አቡነ ልሳነክርስቶስማቴዎስ 2008 .. የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓልን በማስመልከት ያስተላለፉትመልእክት::

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

“ሞት በድል ተዋጠ” /1ቆሮ 15፡54/

በክርስቶስ እጅግ የተወደዳችሁ ምዕመናን፤ ካህናት፤ ወንዶችና ሴቶች ደናግላን፤ መነኮሳት እንድሁም በጎ ፍቃድ ላላችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፡

እንኳን ለ2008ዓ.ም የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ በሰላም አደረሳችሁ እላለሁኝ፡፡ የሰው ልጅ በመሰረቱ ሕልውናውን የሚፈታተኑ  ነገሮችን ይፈራል፡፡ መሸሽም ይሞክራል፡፡ ለምሳሌ ሕመም፤ ድህነት፤ ሞት ወዘተ….ይፈራል፡፡ እንዚህ ነገሮችን የየዕለቱ በማህበረሰብም ሆነ በቤተስብ አልፎም በእምነት ሕይወታችን ያለውን ደስታ ገፈው ጭጋግ የሚያለብሱ ናቸው፡፡ እነሆ በዘመናችን ሰላምን ለሚያደፈረሱ ምክንያቶች ቁጥር እጅግ እየበዛና እየተወሳሰበ በመሄዱ የሞትን ወሬ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ለመፍትሄም የሚነሳሱ ቁጥራቸው እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡

እነሆ ዛሬ የምናከብረው በዚህ በፋሲካ ሌሊት የሚናስብው የእግዚአብሄር ሥራ ስጋችን አልፎ ነፍሳችንን የሚያስፈራው ሞት በድል ተዋጠ፡፡ ኃይሉም ብን አለ፡፡ ፍቅር እንደሆነ የሚናውቀው አምላክ በሞቱ ሞትን ድል ስላደረገ እጅግ ደስ ይበለን፡፡ ላላፈውም ኃጢአታችን ለዛሬውና ገና ለደወፊት ለምንሰራው ኃጢአት ካሳ ይሆን ዘንድ ዋጋ ያለውን ሞት ሞተ፡፡ ቃሉ፡ በመገረፉ ቁስል እኛ ተፈወሰን እንዳለው ዛሬ ምንም እንኳን በምድር ላይ የሰው ልጅ መከራው የበዛ ቢሆንም እነሆ “ሞት ሆይ ሰውን የምትጎዳበት ኃይል የት ነው?” በማለት ሐዋሪያው ጳውሎስ የጠየቀው ጥያቄ (1ቆሮ 15፡55) የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤን በማየቱና መከራዎቻችን ሁሉ እኛ የመጉዳት አቅም የሌላቸውና ክርስቶስ ከእነዚህ ሁሉ ትንሳኤያችን መሆኑን በማየቱ ነው፡፡

ስለዚህ ዛሬ ኑሮን ድህነትን ሕመምን፤ ራስ ወዳድነትን፤ ጥላቻን የምንታገለው ድል አድራጊነታችን በክርስቶስ ትንሳኤ ተረጋግጦ ስለሆነ ስራዎቻችንን የምናከናውነው በደስታ ነው፡፡ እነሆ እንግድህ ክርስቶስ በመከራው በመታዘዙና በትንሳኤው ለቀጣዩ ሕይወታችን የተስፋ ብርሃን አበራልን፡፡

እነሆ ዛሬም በጌታ እኛም ለሌሎች የተስፋቸው መንሰራራት ምክንያት እንዲንሆን ተጠርተናል፡፡ በበዓሉም ሆነ ከበዓሉ ወጭ ድሆችን ማገዝ በሽተኞችንና የህግ ታራሚዎችን መጎበኘት ባህላችን እንዲናደርግ፤ እንዲሁም የይቅርታ መንፈስ በማህበረሰባችን ለማስፈን ተጠርተናል፡፡

በዚህ በዓለ ትንሳኤ አበክሬ ላስታውስ የምወደው የወደፊቱን ተተኪ ልጆቻችን ሕፃናት ነገ የተሻለ ዓለም እንዲኖራቸው ዋና መፍትሄ የሆነውን የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ ወንዶችና ሴቶች ሕፃናት ያለምንም ልዩነት የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ለማድረግ በመንግስታችን እየተደረገ ያለው ጥረት እያደቅሁ ሕብረተሰቡ በበለጠ ማደግ እንደሚገባውና አንድም ወንድና ሴት ሕፃናት ያለትምህርት እንዳይቀሩ ለማድረግ እያንዳንዱ የሕብረሰብ አካልና የሚመለከታቸው ተቋማት ጥረት እንዲያደርጉ ይገባል፡፡

በቅርቡ በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ነዋሪ ሕዝብ ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ ቤተሰቦቻቸውን ወንድሞቻቸውን ሕፃናትን በሞትና በስርቆት ላጡ ወገኖቻችን የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እየገለፅኩ በሐዘናቸው ከጎናቸው እንዲንቆምና አጥፊዎችንም ከጥፋት ድርግታቸው እንዲመለሱ በምንችለው ሁሉ በፍፁም ሰላማዊ መንገድ የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ እንድናፅናናቸው ጥሪዬ እያስተላለፍኩ ይህንን የጭካኔ ተግባር ቤተክርስቲያን በፍጹም ታወግዛለች፡፡ ለሞቱት እግዚአብሔር መንግስቱን እንዲያወርሳቸው ቤተክርስቲያን ትጸልያለች፡፡

በመጨረሻም አልጋ ላይ ለሚገኙ ሕሙማን፤ ለህግ ታራሚዎች፤ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በተላይም የክልላችን ሕዝቦች እንኳን ለ2008ዓ.ም ብርሃነ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

Translate »